(በአባ ዘሚካኤል ዼሬሣ)
ነቢዩ ነህምያ በባቢሎን በሱሳ ግንብ ሳለ፤ ከወንድሞቹ አንዱ አናኒና ሌሎች ከይሁዳ መጡ፡፡ ነቢዩ ነህምያም በይሁዳ ስላሉ ከምርኮ ስለተረፉትና ስለኢየሩሳሌም ከተማ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም እንዲህ አሉት «'ከምርኮ የተረፉት በታላቅ መከራና ስድብ አሉ፡፡ የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈርሶአል፡፡ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋል»፡፡ ይህንን በሰማ ጊዜ ነህምያ ታላቅ የሆነ ሐዘኑን እንደሚከተለው ገለጸ፡፡
«ይህንን ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፤ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፡፡ በሰማይ አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር፡፡... ቃል ኪዳን ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ... የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፣ ዐይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል፡፡ እጅግ ክፉ ሠርተናል ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝከውን ሕግና ሥርዐት አልጠበቅንም፡፡» (ነህ. 1፣ 4-8)፡፡