ደብረ ዘይት የቦታም የበዓልም ስም ነዉ። ቦታዉ ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ የሚገኝ የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ሲሆን ስሙም ደብረ ዘይት (የዘይት ተራራ) ተብሏል። በቅ/ቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ አበይት በዓላት ደግሞ ደብረ ዘይት አንዱ ነዉ። ደብረ ዘይት በዓል ሆኖ የሚከበርበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ሳለ ለቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍፃሜ እና ስለ ዳግም ምጽአቱ ስላስተማራቸዉ በጌታችን ትምህርት መሰረት ነገረ ምጽአቱን (የመምጣቱን ነገር) እንድናስታዉስ ወይም እያሰብን እንድንዘጋጅ ለማድረግ ነዉ።
በዚህች እለት ነገረ ምፅአቱን ለደቀ መዛሙርቱ እንደገለጠ በዓለም መጨረሻም የሚመጣዉ በዘመነ ዮሐንስ፡ በወርሃ መጋቢት፡ በእለተ እሁድ(ሰንበት) መሆኑን ሊቃዉንተ ቤተ ክርስቲያን ያመሰጥራሉ (ምስጢሩን ገልጠዉ ያስተምራሉ)፡፡ ነገር ግን በየትኛዉ ዘመነ ዮሐንስ እንደሚመጣ ሳይገልጥ ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያዉቅ የለም።” ማቴ. 24፡36 ብሏል። ይህን ማለቱም በየዘመኑ የሚነሱ ክርስቲያኖች ሩቅ ነዉ ብለዉ እንዳይዘናጉ ጊዜዉ ሲቀርብ የሚነሱት ደግሞ ደረሰብን ብለዉም እንዳይሸበሩ /እንዳይታወኩ መጠበቅ ነዉ። እንኳን የዓለምን ፍጻሜ የምንሞትባትን እለት እንኳን ሳናዉቃት የምትመጣ ባትሆን ኖሮ ሰዉ በጭንቀት የተሞላ መራራ ሕይወትን በመራን ነበር። ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸዉ ወደ እርሱ ቀርበዉ “የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነዉ? አሉት” ማቴ. 24፡3 እርሱም በስፋትና በጥልቀት ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ ዳግም ምጽአቱ ምልክቶቹን አስተማራቸዉ። በዚያን ጊዜ ምልክቶቹ ሲነገሩ የሚደርሱ ላይመስሉ ይችሉ ይሆናል። የተነገሩትን ምልክቶች ዛሬ ስናያቸዉ ግን ምን የቀረ ነገር አለ ያስብል፤ ምን አልባት ዘንድሮ ወይም በሚቀጥለዉ ዓመት ይመጣ ይሆናል ብሎ ለመጠባበቅ የሚያሳስቡ ሆነዉ እናገኛቸዋለን። የዓለምን ፍጻሜና የጌታችንን ለፍርድ መምጣት የሚያሳስቡትን ዋና ዋና የሆኑትን ምልክቶች ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታቸዋለን።
ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ! ማንም/ምንም እንዳያታልላችሁ ተጠበቁ! የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24
1. የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ይታያሉ
ዲያብሎስ በሰዉ ልጆች ላይ እጅግ ብዙ አስቸጋሪ መከራዎችን ያመጣል፤ የኛ ሕይወት ለእግዚአብሔር በማይመችበት ጊዜ ለዚህ መከራ እንጋለጣለን። ምጥ ሲመጣ አስቀድሞ የምጡ መጀመሪያ ሕመም (ጣር) እንዳለ ሁሉ የዓለምም ፍጻሜ በጣር ነዉ የሚጀምረዉ። ይህንንም ጌታችን በግልፅ አስረድቶናል፦ ጦርና የጦር ወሬ፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ መነሳት፡ ርሃብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ መታየት ለዓለም ፍጻሜ የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ናቸዉ። ከአመጻ ብዛት የተነሳ የብዙ ሰዎች ፍቅርም ትቀዘቅዛለች ብሎናል። እነዚህ ነገሮች በሁሉም ታ በአንድ ጊዜ ላይከሰቱ ይችላሉ፤ ነገር ግን በልዩ ልዩ ቦታዎች ለብዙ ዘመናት ታይተዋል፤ እየታዩም ናቸዉ። ስለዚህ የምጡ ጣር መጀመሪያ ተከናዉኗል/አልቋል። ከምጡ ጣር በኋላ መቼም የማይቀረዉ ነገር ቢኖር ልጅ መዉለዱ ነዉ፤ የምጡ መጀመሪያዎች መከናወናቸዉን በእርግጠኝነት የሚታዩ ስለሆነ አሁን የሚቀረዉና የምንጠባበቀዉ የዚህን ዓለም ፍጻሜ ብቻ ነዉ።
2. ስለ ስሜ በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ መጨረሻ ስለ ስሜ (የክርስቶስ ተከታዮች/ ክርስቲያኖች በመሆናችሁ) በዓለም ዘንድ ትጠላላችሁ ብሎናል። ዓለም ክፉ ስለሚሰራ የጥሩ ነገር ተቃራኒ ሆኖ ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። ጌታችን “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ስራቸዉ ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነዉ። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፡ ስራዉም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እዉነትን የሚያደርግ ግን ስራዉ በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ዮሐ. 3፡ 19-21 እንዳለን በክፉ ስራ ዉስጥ ያለዉ ይህ ዓለም በጎ ስራ የሚሰሩትን የክርስቶስን ተከታዮች ይጠላል። ጨለማ ብርሃንን ብርሃንም ጨለማን እንደሚጠላ ክርስቲያኖች ይህንን ዓለም እንጠላዋለን፤ ይህ ዓለም ደግሞ እኛን ይጠላናል። አሁን ባለንበት ዘመን ክርስትና እየተጠላ፡ እየተናቀ ነዉ ያለዉ። “ባደጉት” ዓለማት ባዶ አብያተ መቅደሶች ቀርተዉ እነሆ እንመለከታቸዋለን፤ ትዉልዱ ክርስትናን ጠልቷል፡ በዓለም ስሜትና በስጋ ፈቃድ ብቻ እየሄደ ነዉ። “ባላደጉት” አገሮች ደግሞ የአንገት በላይ (የማስመሰል) ክርስትና እንጂ እንደ ቅዱስ ቃሉ የሚጓዝ አማኝ ማግኘት እየከበደ መጥቷል። እዉነተኞች አይወደዱም፡ ይገፋሉ፤ ይናቃሉ። ሁኔታዉ የዘመኑ ፍጻሜ እጅግ እየቀረበ መምጣቱን በእርግጥ ያስረዳል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህም በላይ፦ ስለ ስሜ ለመከራ አሳልፈዉ ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል ብሏል። ክርስቲያን በመሆናቸዉ ብቻ ምንም ሳያጠፉና ማንንም ሳይበድሉ ከዘመነ ሰማዕታት ጀምሮ በልዩ ልዩ ሃገራት ክርስቲያኖች ሲገደሉ እስከ አሁን ድረስ አሉ፤ ብዙ ክርስቲያኖች በተለያየ ቦታ ዛሬም ይገደላሉ። ቅዱስ ጳዉሎስ “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፡ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደተጻፈ ነዉ” ሮሜ 8፤36 እንዳለዉ ይህ በቅዱሱ በክርስቶስ ስም መጠላትና መከራ መቀበል ከዓለም የሚጠበቅ የፍፃሜዉ ዘመን ምልክት መሆኑን አዉቀን መዘጋጀትና ከሐዋርያዉ ጋር “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።” ሮሜ 8፤37 እያልን በእምነታችን ፀንተን መጋደል ይገባናል። የክርስቲያኖች ቁጥር እያነሰ ሲመጣ፡ አብያተ ክርስቲያናት ሲዘጉ፡ ሰዉ ሰዉ የሚያሰኘዉን ክብርና ሞገስ ትቶ በግብሩ እንስሳትን ሲመስልና ለረከሰዉ ለዚህ ዓለም ምኞትና ፈቃድ ሲገዛ፡ የቅድስና ሕይወት ሲጠላና ሲናቅ ወዘተ ስናይ ጊዜዉ እየደረሰና የትንቢቱ ቃል እየተሟጠጠ መሆኑን አዉቀን ራሳችንን ከዓለሙ እርሾ እንጠብቅ። ኖህ በዘመኑ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ቢኖርም ራሱን በቅድስና ጠብቆ እንደኖረ (ዘፍ.ምዕ. 6-8) ሎጥም እንዲሁ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ሲኖር በነርሱ ኃጢአት እንዳልተባበረ (ዘፍ. 19) እያስታወስን ከዚህ ዓለም ክፉ ስራ ተለይተን በቅድስና ለመኖር እንጋደል፤ ዓለሙ ስለ እምነታችን ቢጠላንም እኛም ስለ ክፉ ስራዉ ዓለሙን ስለምንጠላዉ ተለያይተን መኖራችን የግድ መሆኑን እንወቅ። ከዓለም በጎ ነገር አንጠብቅ፤ በተለያዩ ሁኔታዎች የሚደርሱብንን ፈተናዎች ሁሉ በትዕግስት እንቀበላቸዉ እንጂ በማማረር ልናዝን አይገባንም፤ ምክንያቱም ስለ ስሜ በዓለም ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ ተብለናልና።
3. የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰዉ ስፍራ ይቆማል
ዲያብሎስ ዓለምን በማርከስ ብቻ ሳይወሰን በፍፃሜ ዘመን በተቀደሰዉ ስፍራ እነኳን ሳይቀር የጥፋትን ርኩሰት ያቆማል። የተቀደሰዉ ስፍራ የተባለዉ በተቀደሰ ሃይማኖት የሚኖሩትን ሃገራት፡ ሕዝቦች የሚመለከት ነዉ። እንደ እስራኤልና ኢትዮጵያ የመሳሰሉትን ሃገራት ዲያብሎስ በብዙ ርኩሰት አሰቃይቷቸዋል። የየሃገራቱን እምነትና ታሪክ ለማጥፋት ብዙ መልእክተኞችን ልኳል፤ ብዙዉንም የእምነትና የቅድስና ስርዓት በርዞአል፤ የቻለዉንም ከነጭራሹ አጥፍቶታል። አሁን እንኳ አምልኮተ እግዚአብሔር በሚፈፀምባቸዉ ቅዱሳት መካናትና ገዳማት እንኳን ሳይቀር በልዩ ልዩ ምክንያት የጥፋት ርኩሰትህ አዉጇል። ይህም የፍፃሜ ዘመኑ አንዱ ምልክት ስለሆነ አንባቢዉ ያስተዉል እንደተባለ የዘመኑን መፍጠን የጊዜዉን መድረስ በመረዳት መዘጋጀት ይገባናል። “በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያለ ወደተራራ ይሽሽ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደሗላዉ አይመለስ” ብሏል ጌታችን መድኃኒታችን ኢይሱስ ክርስቶስ። ተራራ የተባለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። የጊዜዉን መድረስ እያስተዋልን ከፊት ይልቅ በአምልኮ እየተጋን፤ ቃሉን በመስማትና በሕገ እግዚአብሔር በመኖር እየበረታን እንድንሄድ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን መሰብሰብ ያስፈልገናል። በክፉ ቀን ወደ ቤት መሰብሰብ፤መከተት ነዉ የሚጠቅመዉ። በዉጪ ሆነን ስንዘናጋ ቀኑ እንዳይደርስብን እንጠንቀቅ። በክፉ ቀን ከቤቱ ዉጪ የሚሆን ሰዉ ላልታሰበ አደጋ የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ እነደሆነ ሁሉ በዚህ ግራ በገባዉ ሰዉ ከሰዉ በሚነካከስበትና በሚጨካከንበት ዘመን ሁሉን በአንድ ፍቅር አቅፋ የፈቅርን ወተት ወደምትመግበን እናት ቤተ ክርስቲያን የማይሰበሰብ ሰዉ የጊዜዉን እንቅፋት ሁሉ ለማለፍ የሚቸገር መሆኑ የማይቀር ነዉ። ጌታችን፦ “በዚያን ጊዜ ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸዉ” ብሏል። እርጉዞችና የሚያጠቡ የተባሉት ኃጢአትን ያረገዙና የሚያጠቡትን ነዉ። ኃጢአትን በንስሐ ላልተገላገሉ፤ በኃጢአት ላይ ኃጢአት እየጨመሩ ለሚያጠቡ ማለት ኃጢአታቸዉን ለሚንከባከቧት ወዮላቸዉ ማለት ነዉ። ምክንያቱም በኖህ ዘመን የነበሩትን ሰዎች ንስሐ ግቡ ቢባሉ ገና ብዙ ዘመን አለ እያሉ ሲዘናጉ የጥፋት ዉሃ ድንገት መጥቶ ወስዷቸዋል። አሁንም ንስሐ ለመግባት ረጅም ቀጠሮ የሚሰጡ፡ በኃጢአት ላይ ኃጢአት እየሰሩ የሚኖሩ ሰዎች ሳይዘጋጁ ድንገት ቀኑ ይመጣባቸዋል፤ ከዚያ በሗላ ለንስሐ ዕድል ስለማይኖራቸዉ ወዮላቸዉ ተብለዋል። በእርሻ ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደኋላዉ አይመለስ የተባለ አገልጋዮችን ነዉ። “ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግስት የተገባ አይደለም።” ሉቃ. 9፡62 እንዳለ ጌታችን፤ አገልጋዮች የማያስደስቱትን ሁኔታዎች በተለይም የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰዉ ስፍራ አይተዉ ተስፋ ቆርጠዉ ወደኋላ ማፈግፈግ የለባቸዉም፤ ከእነርሱ የሚጠበቅባቸዉን አገልግሎት በፅናት መወጣት ይኖርባቸዋል እንጂ። አገልግሎትን የሚያደነቃቅፉና ወደ ሗላ የሚጎትቱ ብዙ ነገሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ የተቀደሰዉን አገልግሎት ትቶ ወደ ማንም መሄድ አይቻልም (ዮሐ6፡68) በጊዜዉም ያለ ጊዜዉም መትጋትና (2ጢሞ. 4፡2) ወደፊት መገስገስ ያስፈልጋል። ጊዜዉ ይበልጥ አስቸጋሪ በሆነ ቁጥር ከፊት ይልቅ እጅግ እንድንበረታ “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን አጥብቃችሁ ጸልዩ” ነዉ ያለን። የክረምት ሽሽት በዝናቡ፡ በጭቃዉ፡ በድጡ፡ በዉሃዉ ሙላት ወዘተ ብዙ መከራ እንዳለበት ሁሉ ካልተዘጋጃችሁ እንዲሁ ከባድና አስቸጋሪ የሆነ ጊዜ ፈጥኖ ይመጣባችሗልና አጥብቃችሁ ተግታችሁ ጸልዩ አለን። ምክንያቱም የጌታችን መምጫዉ ቀን እጅግ እየቀረበ ሲመጣ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያዉቅ ወደፊትም የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። ይህን የመከራ ጊዜ ስለ ተመረጡ ሰዎች ሲል ጌታ ያሳጥረዋል እንጂ ባያሳጥረዉ ኖሮ ማንም ሊድን ባልቻለም ነበር። ጌታ ቢፈቅድ ከዚያ እንዳያደርሰን፤ ቢያደርስን ደግሞ እንዲያስችለንና እንዲያበረታን በብርቱ መጸለይ አለብን።
4. ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉ
አሁን ዓለምን እያናወጣት ያለዉ የሐሰተኞች ነቢያት ትምህርት ነዉ። ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት በየዘመኑ ተነስተዉ እዉነተኛይቱን ቤተ ክርስቲያን ታግለዋታል፤ ሊያጠፏት ባይችሉም እንኳን ብዙ ልጆቿን ነጥቀዉ አጥፍተዋቸዋል። የነዚህን ሐሰተኞች ሰራተኞች አመጣጥ ከባድ የሚያደርገዉ በተኣምራትና በድንቅ ምልክቶች መምጣታቸዉ ነዉ። ጌታችን እንደተናገረ “ቢቻላቸዉስ የተመረጡትን እንኳን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።” ስለዚህ በምትሐታዊ ምልክቶቻቸዉ የብዙ የዋሐንን ልብ በማታለል ከተቀደሰ እምነታቸዉ እያስኮበለሉ አጥፍተዋቸዋል፤ በማጥፋትም ላይ ይገኛሉ። ስለዚህም ሐዋርያዉ ቅ/ዮሐንስ “ ወዳጆች ሆይ፦ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነዉ እንደሆነ መርምሩ “ 1ዮሐ. 4፡ 1-3 አለን። ቅዱስ ጳዉሎስም “ የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸዉን እየለወጡ ዉሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሰራተኞች ናቸዉ። ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለዉጣልና።” 2ቆሮ. 11፡13-15 ብሏል። ሐዋርያት ሁሉ በየመልእክቶቻቸዉ ከሐሰተኞች አስተማሪዎች እንድንጠበቅ ደጋግመዉ አሳስበዋል። ብዙ ሰዉ ግን በየዋሕነት ስለሚጓዝ የነዚህ ተኩላዎች ሰለባ ሆኗል። ጊዜዉ ክፉ ነዉና የሐሰተኞች ነቢያት መረብ ጠልፎ ወደ ሐሰተኛዉ ክርስቶስ እንዳይወስደን በጥንቃቄ መጓዝ ይጠበቅብናል። ሐዋርያዉ ቅ/ይሁዳ በመልእክቱ ቁ .3 “ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።“ ሲል እንደመከረን በተቀደሰ እምነታችን እስከመጨረሻ ለመጽናት እንጋደል።
5. የሰዉ ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ይመጣል
ክቡር ዳዊት በትንቢት “እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም። እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፡ አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም።” መዝ. 49፡3 እንዳለ ጌታችን በብዙ ክብርና በብዙ `ይል ከሰማይ መላእክት ጋር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። ቅዱሳን መላእክት ለእርሱ የተመረጡትን ከአራቱም ማዕዘን ይሰበስባሉ ፤ በዚያን ጊዜ ከመጀመሪያዉ ሰዉ ከአዳም ጀምሮ እስከ መጨረሻዉ ሰዉ ድረስ ሁላችንም በሕይወተ ስጋ የሰራነዉን ስራ ይዘን በፊቱ እንቀርባለን (2ቆሮ. 5፡10)። ጌታችንም በጎ የሰሩትን ቅዱሳን በቀኙ፤ ክፉ የሰሩትን ኃጥአንን በግራዉ ያቆማቸዉና ፍርዱን ያስተላልፋል (ማቴ. 25፡ 31-መጨ)። በዚህ ዓለም ፈቃድ የተጓዙ ኃጥአን ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጉስቁልና ይጣላሉ። በዚህ ዓለም ክፉ ስራ መንፈሳቸዉን እያስጨነቁ በእምነትና በቅድስና ተጠብቀዉ የኖሩ ጻድቃን ደግሞ በደስታ እየዘመሩ ወደ ማታልፈዉ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ይከማቻሉ። ከዚያ በኋላ በማያልቅ ደስታ ለዘላለም መኖር እነጂ ሐዘን የለም፤ ሃብታምና ድሃ ሃይለኛና ደካማም አይኖርም ።
ያን ጊዜ የእኛ እጣ በየት ይሆን?
በቀኙ ለመቆም እንዲያበቃን ዛሬ እንጋደል።
የቅዱሳን ሐዋርያት መልእክት ፦
“ወደ እግዚአብሔር መንግስት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል…” ሐዋ. 14፡22
“ጻዲቅ በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛዉና ኃጢአተኛዉ ወዴት ይታይ ዘንድ አለዉ?” 1ጴጥ.4፡18 የሚል ነዉ! እንግዲህ እጅግ ባጭሩ የደብረ ዘይትን በዓል የምናከብረዉ እነዚህን እንድናስታዉስና ዝግጅት እንድናደርግ ነዉ።
በዚያ አስፈሪ ቀን በቀኙ ለመቆም እንዲያበቃን የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የርኅርሂተ ኅሊና የድንግል ማርያም አማላጅነት፡ የቅዱሳን ሁሉ ረድኤት አይለየን፤ አሜን።
አዘጋጅ፦
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ
ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማዕከል
የሆላንድ ቀጠና ማዕከል ትምህርት ክፍል