«ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ እንዳያስቷችሁ ተጠንቀቁ ምጽአት እንደ ደረሰ ምሳሌውን /ምልክቱን/ ከበለስ እወቁ ሰማይ ከምድር ጋር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም አላቸው» እያለ ጌታ በደብረ ዘይት ምሥጢረ ምጽአቱንና የዓለም ኅልፈትን ነገር ለማስተማሩና ከሐሰተኞች ነቢያት እንዲጠበቁ ለማስጠንቀቁ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፡፡
የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ቁ 1 እስከ መጨረሻው በማርቆስ ወንጌል ምዕ 13 ከቁጥር 1 እስከ መጨረሻው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ቁጥር 5 እስከ መጨረሻው ተጽፎ ይገኛል፡፡ ደብረ ዘይት በኢየሩሳሌም ምሥራቅ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ጌታ በዚህ ዳግመኛ የመምጣቱን ትምህርት እንዳስተማረ ሁሉ ያረገውም በዚያ ተራራ ነው፡፡
1ተሰ 4.13-18
«ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ተስፋ እንደሌላቸው እንደሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን፡፡ ኢየሱስ እንደሞተና እንደተነሳ ካመንን እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፡፡ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፡፡ ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፤ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሳሉ፡፡ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን፡፡ ስለዚህ እርስ በእርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ፡፡»
2ጴጥ3.7-15
«አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል፡፡ እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን አንደሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ፡፡ ለአንዳንዶቹ የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለተስፋ ቃሉ አይዘገይም፡፡ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሳል፡፡ የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፡፡ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል፡፡
ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል፡፡ ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደምን ልትሆኑ ይገባችኋል) ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን፡፡
ስለዚህ ወዳጆች ሆይ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደሆነ ቁጠሩ፡፡»
የሐዋ.ሥራ 24.1-22
«ከአምስት ቀን በኋላም ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዡ አመለከቱት፡፡ በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ ይከሰው ዘንድ ጀመረ፡፡ እንዲህ እያለ «ክቡር ፊልክስ ሆይ በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየሥፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፣ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን፡፡ ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡ ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፡፡
ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፡፡ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ፡፡ አይሁድም ደግሞ ይህ ነገር እንዲሁ ነው እያሉ ተስማሙ፡፡ ገዡም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ መለሰ እንዲህ ሲል፡- ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፡፡ እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣሁ ከአሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ፡፡ ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኩራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም፡፡ አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሱ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ፡፡
ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ፡፡ ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤ ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰባሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ፡፡ ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደሆነ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ፡፡ ወይም በመካከላቸው ቆሜ ዛሬ ስለሙታን መነሳት በፊታችሁ በእኔ ይፈርዱብኛል ብዬ ከጮኽሁት ከዚህ ከአንድ ነገር በቀር በሸንጎ ፊት ቆሜ ሳለሁ ከእኔ አንድ ዓመጻ ያገኙ እንደሆን እነዚህ ራሳቸው ይናገሩ፡፡
ፊልክስ ግን የመንገዱን ነገር አጥብቆ አውቆአልና የሻለቃው ሉስዮስ በወረደ ጊዜ ነገራችሁን እቆርጣለሁ ብሎ ወደፊት አዘገያቸው፡፡»
መዝ 49፡3
እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ
ወአምላክነሂ ኢያረምም
እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡
እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፡፡
አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፡፡
እሳት በፊቱ ይቃጠላል፡፡
ማቴ 24.1-36
«ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፡፡ ደቀመዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ፡፡ እርሱ ግን መልሶ ይህን ሁሉ ታያላችሁን) እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው፡፡ እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው ንገረን ይህ መቼ ይሆናል) የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው) አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡ ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ አትደንግጡ፡፡ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤ ራብም ቸነፍርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡
በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ ይገድሉአችሁማል፣ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁለ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሳሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዓመፃም ብዛት የተነሳ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡ እስከመጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል፡፡ ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፡፡ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል፡፡
እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፡፡ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤ በሠገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፡፡ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደኋላው አይመለስ፡፡ በዚያችም ወራት ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፡፡ ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፡፡ በዚያን ገዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታለቅ መከራ ይሆናልና፡፡ እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ፡፡
እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ፡፡ እንግዲህ እነሆ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ አትውጡ፤ እነሆ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ አትመኑ፡፡ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ፡፡ ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ፡፡ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፡፡ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ፡፡ ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ታወቃላችሁ፡፡ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ፡፡ እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ አስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፡፡ ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም፡፡ ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም፡፡»
ቅዳሴ - ዘአትናቴዎስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር